የሕክምና ባለሙያዎች ብቁ አለመሆንና ጤና ተቋማት በኃላፊነት አለመስራት ለአገልግሎት ጥራት እንቅፋት እየሆኑ ነው

67
ባህር ዳር  አምሌ 6/2010 የሕክምና ባለሙያዎች ብቁ አለመሆንና የግል ጤና ተቋማት በኃላፊነት አለመስራት ለሕብረተሰቡ ጥራት ያለው የጤና አገልግሎት ለመስጠት እንቅፋት እንደሆነበት የአማራ ክልል ጤና ጥበቃ ቢሮ ገለጸ። ቢሮው የበጀት ዓመቱን የ11 ወራት የዕቅድ አፈጻጸም ለክልሉ ምክር ቤት ባቀረበበት ወቅት በምክር ቤቱ አባላት የሕክምና አሰጣጥ ጥራት እየወረደ መምጣቱንና የአግልግሎት አሰጣጥ ክፍተት መስተዋሉ ተገምግሟል። የመጠቀሚያ ጊዜያቸው ያለፈባቸው መድኃኖቶችም በስፋት አገልግሎት ላይ እየዋሉ እንደሚገኙና ታካሚዎቹ ከእንግልት በዘለለ ለሕመማቸው ተገቢ መፍትሄ እያገኙ አለመሆናቸው በምክር ቤቱ አባላት ተገልጿል። የክልሉ ጤና ጥበቃ ቢሮ ኃላፊው ዶክተር አበባው ገበየው በጉባኤው ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽ እንዳሉት ጥራት ያለው አገልግሎት ላለመሰጠቱ የተለያዩ ምክንያቶች ቢኖሩም የባለሙያዎች የአቅም ክፍተት ዋነኛው ችግር ነው። በክልሉ ካሉ ከ46 ሺህ በላይ የጤና ባለሙያዎች መካከል 70 በመቶ የሆኑት የትምህርት ደረጃቸው ዲፕሎማ መሆኑ አገልግሎቱን በተሻለ ጥራት ለመስጠት እንቅፋት እንደሆነም አስረድተዋል። በዘርፉ የበቁ ባለሙያዎችን ማፍራት እስካልተቻለ ድረስ ሕብረተሰቡ በሚፈልገው ደረጃ ጥራት ያለው የሕክምና አገልግሎት ለመስጠት አስቸጋሪ እንደሚሆንም ዶክተር አበባው አመልክተዋል። " ጥራት ያለውና የተገልጋዩን ፍላጎት ማርካት የሚያስችል የሕክምና አገልግሎት መስጠት እንዲቻል በክልልና በአገር ደረጃ ለዘርፉ ትኩረት ሰጥቶ ብቁ ባለሙያዎችን ማፍራት ያስፈልጋል" ብለዋል። ዶክተር አበባው እንዳሉት የመጠቀሚያ ጊዜ ያለፈባቸው መድኃኒቶች በመንግስት የጤና ተቋማት ባይኖሩም የግል ጤና ተቋማት እነዚህን መድኃኒቶች እንደሚጠቀሙ በተደረገ ቁጥጥር ተረጋግጧል። ባለፉት አስር ወራት በ30 ሺህ 629 የመድኃኒት ችርቻሮ ደርጅቶች፣ በተለያዩ የመንግስትና የግል ጤና ተቋማት፣ በምግብ ተቋማትና በጤናና ጤናነክ ተቋማት ቁጥጥርና ክትትል መደረጉንም አስረድተዋል። በእዚህም 89 የተለያየ ደረጃ ባላቸው የጤና ተቋማት፣ 27 የመድኃኒት ችርቻሮ ድርጅቶችና 157 የተለያዩ የምግብና ጤናነክ ተቋማት ላለፉት ጥፋት ማስጠንቀቂያ እንደተሰጣቸው ገልጸዋል። ከእዚህ በተጨማሪ በ31 የምግብ፣ የጤናና የመድኃኒት ችርቻሮ ደርጅቶች ላይ እገዳ የተደረገ ሲሆን በሌሎች 37 ድርጅቶች ደግሞ የፈቃድ ስረዛ እርምጃ መወሰዱን ዶክተር አበባው አስታውቀዋል። የጤና አግልግሎት ጥራትን ማስጠበቅ የሚቻለው በአንድ ተቋም ጥረት ብቻ ባለመሆኑ መንግስት ብቁ ባለሙያን ማፍራት ላይ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እንዲሰራም ጠይቀዋል። ቢሮው የመጠቀሚያ ጊዜ ያለፈባቸውን መድኃኒቶች የሚሸጡና አገልግሎት ላይ የሚያውሉ ተቋማትን ተቆጣጥሮ ተገቢ እርምጃ በመውሰድ በኩል የጀመረውን ሥራ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ዶክተር አበባው ለምክር ቤቱ አስታውቀዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም