የትኛውም አገር የኮቪድ-19 ወረርሽኝ እንዳበቃለት አድርጎ ማየት የለበትም... ዶክተር ቴዎድሮስ አድሃኖም

76

አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 27/2012(ኢዜአ) የትኛውም አገር የኮቪድ-19 ወረርሽኝ እንዳበቃለት አድርጎ ማየት የለበትም ሲሉ የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ቴዎድሮስ አድሃኖም ገለጹ።

ወረርሽኑን ለማሸነፍም በአንድነት መቆም ይገባል ብለዋል።

የዓለም የጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ቴዎድሮስ አድሃኖም የኮቪድ-19 ወረርሽኝ የተከሰተበትን ስምንተኛ ወር በማስመልከት የተንቀሳቃሽ ምስል መልዕክት አስተላልፈዋል።

"የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በተከሰተበት ስምንተኛ ወር ላይ በምንገኝበት ወቅት ሰዎች በመሰላቸት ወደ ቀደመው የኑሮ ሁኔታ የመመለስ አዝማሚያ እያሳዩ ነው" ብለዋል ዋና ዳይሬክተሩ።

አገራትም ቢሆኑ በተመሳሳይ ወረርሽኙ አብቅቷል ወደሚል ማስመሰል ውስጥ እየገቡ በመሆኑ ይሄም ተገቢነት እንደሌለው ነው የተናገሩት።

ሁሉም አገራት ህብረተሰቡና ግለሰቦች ሙሉ ትኩረታቸውን ኮሮናቫይረስን የመከላከልና የመቆጣጠር ተግባር ላይ ማድረግ እንደሚገባቸውም ዶክተር ቴዎድሮስ ተናግረዋል።

ለዚህም አራት ወሳኝ የሆኑ ነገሮችን ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገ ነው የጠቆሙት።

የኮቪድ-19 ወረርሽኝ የስርጭት መጠን የሚጨምሩ ሁነቶችን ከማከናወን መቆጠብ የመጀመሪያው ጉዳይ መሆኑን አመልክተዋል።

በብዙ አገራት በስታዲየሞች ባሉ መሰብሰቦች፣ በምሽት ክበቦች፣ በእምነት ተቋማትና በሌሎች ሁነቶች ወረርሽኙ ዳግም መቀስቀሱንና ይሄን መቆጣጠር እንደሚገባም ገልጸዋል።

"ለአደጋ ተጋላጭ የሆኑ የማህበረሰብ ክፍሎችን ከኮሮናቫይረስ በመጠበቅ የሞት መጠንን መቀነስ ሁለተኛው ተግባር ነው" ብለዋል።

በዕድሜ የገፉ ሰዎች፣ ተጓዳኝ የጤና ችግር ያለባቸውና የሥራ ባህሪያቸው ለቫይረሱ ተጋላጭ የሚያደርጋቸው ሰዎች ልዩ ትኩረት እንደሚያሻቸውም ነው ዶክተር ቴዎድሮስ ያስረዱት።

ግለሰቦች ራሳቸውንና ሌሎችን መጠበቅና የጥንቃቄ ተግባራትን ማከናወን ሌላኛው ወሳኝ ጉዳይ እንደሆነም አክለዋል።

"ቢያንስ አንድ ሰው ከሌሎች ሰዎች አንድ ሜትር መራቅ፣ እጅን በመደበኛነት መታጠብ፣ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል ማድረግ ይገባል" ብለዋል።

ሰዎች በቂ አየር በማይዘዋወርባቸውና ህዝብ በብዛት የሚሰበሰብባቸው ቦታዎች ካለመገኘት ባለፈ የቅርብ ርቀት ግንኙነቶችን መተው እንደሚገባቸው ተናግረዋል።

መንግስታት የኮሮናቫይረስ ታማሚዎችን መፈለግ፣ ለብቻቸው ማስቀመጥ፣ መንከባከብ እና በቫይረሱ ከተያዙ ሰዎች ጋር የቅርብ ግንኙነት ያላቸውን ሰዎች ወደ ለይቶ ማቆያ የማስገባት ሥራን በተቀናጀ መልኩ ማከናወን እንዳለባቸውም ገልጸዋል።

ከሁሉም በላይ የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ብሔራዊ አንድነትና ዓለም አቀፍ ትብብር አስፈላጊ መሆኑን ነው ዶክተር ቴዎድሮስ ያመለከቱት።

የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በታህሳስ ወር 2012 ዓ.ም በቻይና ሁቤይ ግዛት ውሃን ከተማ መከሰቱ ይታወቃል።

ይሄ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ በዓለም አቀፍ ደረጃ በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከ25 ነጥብ 7 ሚሊዮን ሰዎች መሻገሩን እንዲሁም ከ857 ሺህ በላይ ዜጎች መሞታቸውን ከአሜሪካው የጆን ሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ የመረጃ ቋት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

ከ17 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ደግሞ ከቫይረሱ አገግመዋል።

በአፍሪካ እስከ ትናንት ድረስ ከ1 ነጥብ 2 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በኮሮናቫይረስ መያዛቸውንና ከ29 ሺህ በላይ ሰዎች መሞታቸውን የአፍሪካ በሽታ መከላከልና መቆጣጠር ማዕከል መረጃ ያሳያል።

ከ987 ሺህ በላይ ሰዎች ደግሞ ከቫይረሱ አገግመዋል።

በኢትዮጵያም በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 53 ሺህ 304 የደረሰ ሲሆን 828 ሰዎች በቫይረሱ ምክንያት መሞታቸው ከጤና ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

አስካሁን ድረስ 19 ሺህ 487 የሚሆኑ ሰዎች ደግሞ ከቫይረሱ አገግመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም