የሐረርን የፍቅር የሰላምና የመቻቻል ከተማነቷን ማደስ ቀዳሚ ተግባር ይሆናል

ሐረር ህዳር 9/2011 ሐረር የፍቅር፣ የሰላምና የመቻቻል ከተማነቷን የማደስ ተግባር ቀዳሚ አድርገው እንደሚሰሩ አዲሱ የሐረሪ ህዝብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ አስታወቁ።

በአገር አቀፍ ደረጃ የተጀመረው የህዝብን ሀብት በመዝረፍና ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት በመፈጸም የተጠረጠሩ ግለሰቦችን በመያዝ ለፍርድ እንደሚያቀርቡ ገልጸዋል።

ርዕስ መስተዳድሩ ዛሬ ከክልሉ አመራር አባላት፣ ከሀይማኖት አባቶች፣ ከአባገዳዎችና ከህዝብ አደረጃጀት አባላት ጋር ተዋውቀዋል።

በዚሁ ወቅት ባደረጉት ንግግር አዲሱ አመራር በብስለትና በእውቀት፣ በመተጋገዝ፣ በአንድነትና በአዲስ መንፈስ የመስራት አስፈላጊነትን አጽንኦት ሰጥተውታል።

የሐረሪ ህዝብ ክልል የፍቅርና የሰላም ከተማነቷ በመታደስ እንደቀደመው እንዲሆን አበክረው እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

የሀረሪ ነዋሪዎቿ፣ ሀረርና የአጎራባቾቿ ህዝቦች በደም የተሳሰሩና ጠንካራ መስተጋብር እንዳላቸው ጠቁመው፤ በቀጣይ የከተማ ከተማ፣  የከተማ ገጠር ግንኙነትም እንደሚካሄ አክለው ገልጸዋል።

በአገር አቀፍ ደረጃ የተጀመረውን ለውጥ በሀረር ክልል መዘግየቱ ይቅርታ እንደሚያስጠይቅም ነው ያመለከቱት።

የህዝብ ሀብት የዘረፉ፣ ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት በመፈጸም የተጠረጠሩ ግለሰቦችን በመደመር እሳቤ ለህግ ማቅረብ ቀዳሚ ተግባራቸው እንደሚያደርጉት ተናግረዋል።

ለሰላም፣ ለፍቅርና ለህግ የበላይነት መረጋገጥ ህዝቡ ከጎናቸው እንዲሆንም ጥሪ አቅርበዋል።