የድጋፍ ሰልፉ ያለ ፀጥታ ችግር እንዲካሄድ ዝግጅት ተደርጓል

54
አዲስ አበባ ሰኔ 15/2010 በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ የሚመራውን መንግስት በመደገፍ ነገ በመስቀል አደባባይ የሚደረገው ሰልፍ ያለ ፀጥታ ችግር እንዲጠናቀቅ ዝግጅት መደረጉን ፖሊስ አስታወቀ። የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን እንዳስታወቀው የድጋፍ ሰልፉ በሰላም እንዲጠናቀቅ ከፌዴራል ፖሊስና ከሌሎች የፀጥታ ኃይሎች ጋር በመተባበር ዝግጅት ተደርጓል። የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ ትብብር፤ በተለይም ወጣቱ በኃላፊነት መንፈስ እና በሠላማዊ መንገድ እንዲንቀሳቀስ ኮሚሽኑ ለኢዜአ በላከው መግለጫ አሳስቧል። የድጋፍ ሰልፉ በሚካሄድበት አካባቢ ስለት ያላቸው ነገሮች፣ የጦር መሳሪያዎችና በህግ የተከለከሉ ማናቸውም ቁሳቁሶች ወደ ሰልፉ ቦታ ይዞ መምጣት የተከለከለ መሆኑንም አስታውቋል፡፡ ሰልፉ ተጀምሮ እስኪጠናቀቅ ወደ መስቀል አደባባይ በሚያስገቡ መንገዶች ተሽከርካሪ ማቆም እንደማይቻልና መንገዶች ለጊዜው ለተሽከርካሪ ዝግ መሆናቸውንም ጠቁሟል፡፡ ህብረተሰቡ ሌሎች አማራጭ መንገዶችን በመጠቀም እንደከዚህ ቀደሙ ትብብር እንዲያደርግም ነው ኮሚሽኑ ጥሪ ያስተላለፈው። ከዚህ ቀደም በከተማዋ ኃይማኖታዊና ብሔራዊ በዓላት በሠላም እንዲከበሩ ህብረተሰቡ ከፀጥታ ኃይሉ ጋር በመተባበር ወሳኝ ስራ ማከናወኑን ጠቅሷል፡፡ አሁንም ሰልፈኞች የፀጥታ ኃይሎች በሚያደርጉት ፍተሻ የተለመደ ትብብራቸውን እንዲያደርጉ ጥሪ ያቀረበ ሲሆን የትራፊክ መጨናነቅ እንዳይፈጠርም አሽከርካሪዎች ተለዋጭ መንገድ እንዲጠቀሙ ጠይቋል። ህብረተሰቡ የፖሊስን አገልግሎት ለማግኘትም ሆነ አጠራጣሪ ነገሮች ሲያጋጥሙት መረጃ ለመስጠት 991 ወይም 816 ነፃ የስልክ ቁጥሮችን መጠቀም እንደሚችሉም ነው የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ያስታወቀው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም